የጥናቱ ዋና ዓላማ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎች በአማርኛ ቋንቋ ምርምር የማድረግ አመለካከትን፣ ፍላጎትንና ተግዳሮቶችን መፈተሽ ነው። ይህን ዓላማ ለማሳካት መጠናዊ የምርምር አይነትንና ገላጭ ዳሰሳዊ የምርምር ንድፍን በመከተል ተከናውኗል፡፡ በጠቅላይ ንሞና ከተመረጡ 10 በአማራ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች 379 መረጃ ሰጪዎችም በተራ ዕጣ ንሞና ተመርጠው በጽሁፍ መጠይቆች መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ የተሰበሰቡት መረጃዎችም የተለያዩ የአስተማማኝነትንና የፓራሜትራዊ ቴስቶች እሙኖችን መሟላታቸው ከተፈተሸ በኋላ እንደመሰረታዊ ጥያቄዎቹ ባህርያት በመቶኛ፣ በአማካይ ውጤት፣ በመደበኛ ልይይትና በነጠላ ናሙና ቲቴስት እየተሰሉ ተተንትነዋል፡፡ ከመረጃ ትንተናውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎች በአማርኛ ቋንቋ ምርምር ስለማድረግ ያላቸውን አመለካከት በአዎንታም በአሉታም የሚገለጽ መንታ መንገድ ላይ የቆመ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከዚህም ሌላ በአማርኛ ቋንቋ ምርምር ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ተረጋግጧል፡፡ በተለይም ለሳይንስ፣ ለቴክኖሎጂና ለአካዳሚ ዕውቀቶች ልውውጥ ከውጭ ቋንቋዎች ይልቅ አማርኛ ቋንቋ መጠቀም እንደሚፈልጉና ቋንቋውን በምርምር ቋንቋነት መጠቀም ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል የሚል ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸው ምቹ ሁኔታ እንዳለ አሳይቷል፡ በአንጻሩ ግን በአማርኛ የሚጻፉ ምርምሮች የህትመት፣ የስልጠና፣ የተቋማት ማበረታቻ፣ የምርምር ፖሊሲዎች አለመኖር በቋንቋው ምርምር የማድረግ ፍላጎታቸውን ዝቅ ያደረጉ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም ምርምርን በእንግሊዝኛ ቋንቋ መስራት የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ እንቅፋት መሆኑን፣ የምርምር ውጤቶችን ወደተግባር ለመለወጥ አዳጋች ማድረጉን፣ አገርኛ ቋንቋዎች ወደምርምር ቋንቋነት እንዳያድጉ ማዳከሙን፣ የእውቀት ሽግግር እዳይኖር እንቅፋት መፍጠሩን፣ የአገር በቀል እውቀቶችን ለመጠቀም መሰናክል መሆኑን፣ ተመራማሪዎች አለማቀፋዊ ተወዳዳሪ ሆነው በማሳተም የደረጃ ዕድገት በወቅቱ እዳያገኙ እንቅፋት መፍጠሩን፣ ብሎም ጥራት ያለው ምርምር እንዳይጽፉ ጫና ማሳደሩን ያረጋገጠ ውጤት ተገኝቷል፡፡ ከምርምሩ ግኝት በመነሳትም የተለያዩ አስተያየቶችና የመፍትሄ ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡
ደሴ et al. (Sat,) studied this question.