የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ ሀገር በቀል የግእዝ ስነጽሑፍ የሱስን ጠንቅነት ከማስረዳት አንጻር ያለውን ፋይዳ መተንተን ነው፡፡ በዚህ መሠረት ዓይነታዊ የጥናት ንድፍ የጭብጥ ይዘት ትንተናን የተጠቀመ ሲኾን አስፈላጊ የኾኑ መረጃዎች ከቀዳማይ እና ከካልኣይ ምንጮች ተሰብስበዋል፡፡ መረጃዎቹም የተሰበሰቡት በሰነድ ፍተሻ ሲኾን ከገድላቱ እና ከድርሳናቱ ውስጥ የተገኙትን መለያዎች (codes) መሠረት በማድረግ ወደ አስራ አንድ ንዑሳን ጭብጦች ከተመደቡ በኋላ ወደ ስድስት ዐበይት ጭብጦች ተመድበው ተተንትነዋል፡፡ የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው ከአደንዛዥ ዕፀዋት ዕፀ ፋርስ፣ ትንባሆ፣ ጫት እና ቡና ፤ ከአልኮል ጠጅ እና ጠላ በተደጋጋሚ በሱስ አምጭነት የተገለጹ ሲኾኑ ማኅበረሰቡ ከሱስ እንዲርቅ የተጻፉ አስተምህሮቶች የሰይጣን ሥራ እንደሆነ እና ሰይጣን እንደዘራው፣ የክርስትና ባህል እንዳልኾነ፣ የተረገመ፣ የተወገዘ እና የረከሰ ዕፅ እንደኾነ የሚሉት ሲኾኑ የሱስ አምጪ ዕፀዋት እና የአልኮል መዘዝ ደግሞ ነፍስ እንደሚያስኮንን፣ በስጋ ሞት እንደሚያመጣ፣ ከአምልኮ እግዚአብሔር እንደሚያርቅ፣ ራስ ህመም፣ ስርቆት፣ ዝሙት፣ ትዕቢት እና መግደል ሊያስከትል እንደሚችል ተገልጧል፡፡ ወደሱስ እንዳይገባ እና ከሱስ እንዲወጣ የተቀመጡ አስተምህሮቶች ደግሞ እንዳይሳሳቱ ማስተማር /መምከር/፣ በአቻ ግፊት ወደሱስ እንዳይገቡ ግንዛቤ መፍጠር፣ ንስሐ እንዲገቡ ማድረግ ሲኾኑ በገድላቱ እና በድርሳናቱ የተዘረዘሩት አደንዛዥ ዕፀዋት (ሱስ አምጪ ዕፀዋት) እና አልኮል በሳይንስ እይታ ሲታዩ መጻሕፍቱ እንደተናገሩት መዘዛቸው የከፋ እንደኾነ እና ለተለያዩ የጤና፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ ችግሮች ምንጭ እንደኾኑ ይናገራል፡፡ ስለዚህ ሀገር በቀል የግእዝ ስነጽሑፍ በአጠቃላይ ስለሱስ ጠንቅነት በተለይ ስለሱስ አምጪ ዕፀዋት እና አልኮል ምንነት እና መዘዝ ከማስተማር አንጻር ከፍ ያለ ፋይዳ እንዳለው ጥናቱ ያሳያል፡፡
ሙሉ ዓለምነው (Sun,) studied this question.