የዚህ ጥናት ትኩረት ጀግና እና ጀግንነት በጃቢ ጠህናን ወረዳ ማህበረሰብ የቀረርቶና የፉከራ ቃል ግጥሞች ውስጥ እንዴት እንደተገለጹ፣ ምን ተብለው እንደተገለጹ መመርመር ነው፡፡ ጥናቱ ጀግና እና ጀግንነት የሚሉ ቃላትን እንደ ጽንሰ ሀሳብ በመውሰድ በተፈጥሯዊ አውዳቸው በተከወኑ የተመረጡ የቀረርቶና የፉከራ ግጥሞችን ተንትኗል፡፡ ጥናቱ ዓይነታዊ ሲሆን ገላጭ የምርምር ዘዴን በመጠቀም የተሰራ ነው፡፡ መረጃዎች ቀረርቶና ፉከራ በተከወነባቸው አውዶች ምልከታና ቃለ መጠይቅና በማድረግ ተሰብስበዋል፡፡ ከተሰበሰቡት መረጃዎች ውስጥ ለጥናቱ አላማ ተስማሚ የሆኑ ቃል ግጥሞች ተለይተዋል፡፡ እነሱም በይዘት ተተንትነው በገለጻ ስልት ቀርበዋል፡፡ ከትንተናው ውጤት መረዳት እንደተቻለው ለጃቢ ጠህናን ወረዳ ማህበረሰብ ጀግንነት ማለት ለወዳጅ ደጀን፣ መከታ፤ ለጠላት የማይበጅ ነገር አዋቂ፤ አገርና ወንዝ አሳፋሪ፣ ወገን ዘመድ ሰብሳቢና ጠባቂ፤ ሀገር ሲወረር ዘማች፣ ተኳሽ፤ በሰላም አራሽና አምራች፣ በችግር ጊዜ ቀድሞ ደራሽና ችግር ፈቺ መሆን ማለት ነው፡፡ ከዋኞች በግጥሞቻቸው ጀግና ብለው የሚያወድሷቸው ሰዎች በብዛት አባታቸውን፣ ወንድማቸውንና ሌላ የስጋ ዘመቸውን ነው፡፡ እነዚህ ጀግኖች በህይወት ቢኖሩም ባይኖሩም ስማቸው፣ ተግባራቸውና ምግባራቸው ይወሳል፡፡ በመሆኑም የቀረርቶና የፉከራ ግጥሞች የቀደሙ የማህበረሰብና የሀገር ባለውለታዎችን ጀግንነት በመዘከር፣ የአሁኑ ትውልድና በማስተማር፣ ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣ በመቆጣጠርና በማጠንከር ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ጥልቅና ሰፊ ጥናት ቢካሄድባቸው የሚል የይሁንታ ሀሳብ ተጠቁሟል፡፡
ሥራዬ እንዳለው ውበቴ (2026) studied this question.